ለመምህራንና ለትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ብቃት ምዘና በከተማ አቀፍ ደረጃ ግንቦት 1 ቀን የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ፡፡

news39
news40 news41

(ሚያዚያ 29 ቀን 2016 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በጋራ በመሆን የሚሰጠውን ከተማ አቀፍ የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ብቃት ምዘና አፈጻጸምን አስመልክቶ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ምዘናው መንግስት ለትምህርት ጥራትና መሻሻል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በተሻለ ለመምራት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው አካላት በመሆናቸው ምዘና መደረጉ ተገቢና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዋነኛው ሂደት ነው ብለዋል፡፡ ዶክተር ዘላለም አያይዘውም ፈተናውን በተሳካ መልኩ ለማካሄድ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ በበኩላቸው ምዘናው የመምህራንን የሙያ ብቃት ለማሳደግና እውቅና ለመስጠት ከማስቻሉም በላይ መምህራንና የትምህርት አመራሩን በበቂ ስነ-ልቦና ለማስተማርና ለመምራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ የምዘናውን አካሄድ ውጤታማ ለማድረግም የትምህርት አመራሩና የክፍለከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊዎች ለተፈታኞች የሚሰጡ ቅድመ ምዘና ገለጻዎች ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

ምዘናው በፈቃደኝነት ለተመዘገቡ 18 ሺ 591 ለሚሆኑ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ሃሙስ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም በተመረጡ የመፈተኛ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ እንዲሁም በምዘናው ወቅትም ተመዛኞች ስልክም ሆነ ማንኛውንም ኤሌክትሮኒክስ ግብአቶች ይዘው ፈተና ክፍል መግባት እንደማይችሉ ፣ ተመዛኞች የታደሠ መታወቂያ ይዘው መገኘት እንደሚጠበቅባቸው ፣ ተመዛኞች ፈተናው ከመጀመሩ በፊት 1:00 ሠዓት ቀደም ብለው (1:30) ላይ የምዘና መስጫ ቅጥር ግቢ ውስጥ መገኘት እንዳለባቸው እና አርፍዶ መግባት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ፣ የትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት አባላት ፣ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ ፣ የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ደቻሳ ፣ የባለስልጣን መስራቤቱ ማኔጅመንት አባላት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳና አባላት ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እንዲሁም የሁለቱም ተቋማት የክፍለ ከተማ ት/ጽ/ቤት ሀላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ምንጭ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ት/ቢሮ