ለስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች የመማር ብቃት ምዘና ተሰጠ፡፡

(ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም)የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በዛሬው ዕለት ከየቅርንጫፉ በናሙና በተመረጡ የትምህርት ተቋማት ሲካሄድ የነበረውን የስድስተኛ ክፍል የመማር ብቃት ምዘና ሲሰጥ በነበረበት የትምህርት ተቋማት ላይ ከማዕከል እና ከቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተመረጡ አስተባባሪዎች መርሃ-ግብሩን ሲከታተሉ ነበር፡፡

የባለስልጣኑ የአራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የእውቅና ፍቃድ እድሳት ዳይሬክተር ዳይሬክቶሬት የሆኑት ወ/ሮ ማርታ ካሳዬ በሳቸው በኩል ያለውን የምዘና ሂደት እንደገለጹት ምዘናው ለተማሪዎች ከመሰጠቱ በፊት ለ6ኛ ክፍል መምህራን እና ርዕሰ መምህራን በምዘናው ዙሪያ ገለፃ መደረጉን የገለጹ ሲሆን ተማሪዎችንም የመለየት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

photo_2024-11-13_22-59-31 photo_2024-11-13_22-59-46

በአራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምዘናውን ለመስጠት 6 የትምህርት ተቋማት በናሙና በመምረጥ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ተማሪዎች ምዘናውን መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ምዘናው የትምህርት ሂደቱን ለመለካት የተዘጋጀ በመሆኑ የትምህርት ጥራት ውጤታማነትን ለመለካት እና ለማረጋገጥ ጠቀሜታው ከፍተኛ ሲሆን የተገኘውም ውጤት ግብአት ለባለድርሻ አካላት ይቀርባል ብለዋል፡፡

ምዘናውን ሲያከናውኑ ያገኘናቸው የዳግማዊ ሚኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ናደው ባዩ በሰጡት አስተያየት ምዘናው መካሄዱ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው የትምህርት ተቋማት ያላቸውን ክፍተት የሚያዩበት እና ማስተካከል ያለባቸውን ነገር እንዲያስተካክሉ ከመርዳቱ ባሻገር ለትምህርት ጥራት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

photo_2024-11-13_22-59-35 photo_2024-11-13_22-59-50

በምዘናው ዝግጅት ላይ በሰጡት አስተያየት ምዘናው ተማሪዎች ትምህርት በሌላቸው ቀን ቢሆን እንዲሁም ለትምህርት ቤቱ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ሰፊ ጊዜ ቢሠጥ የሚል አስተያየት ሠጥተዋል፡፡
የአቡነ ጎርጎርዩስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ማርቆስ ጌታሁን በበኩላቸው በሳይንሳዊ መልክ ምዘናው ተዘጋጅቶ መካሄዱ ለስርዓተ ትምህርት ክለሳ እና በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

photo_2024-11-13_22-59-42 photo_2024-11-13_22-59-38

ምዘናው መካሄዱ ተገቢ እና ወቅታዊ ሲሆን ለተቋማቸውም ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ተማሪዎች ምን ያህል አውቀው ከክፍል ክፍል ይሸጋገራሉ የሚለውን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት ስራ የጋራ በመሆኑ የተማሪዎች ውጤት ላይም በጋራ በመገምገም መሰራት ያሉባቸውን ስራዎች መስራት እንዲችሉ ተሳትፎአቸውን እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል፡፡ የመማር ብቃት ምዘናው በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ የማስተማርያ ቋንቋ እንዲሁም በ3 የትምህርት አይነቶች መሰጠቱ ታውቋል፡፡