ባለስልጣኑ የተቋማት የእውቅና ፍቃድ እድሳት አፈፃፀም እና የድንገተኛ ኢንስፔክሽን ግኝት ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት አቀረበ፡፡

(ህዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የተቋማት የእውቅና ፍቃድ አፈፃፀም እና የድንገተኛ ኢንስፔክሽን ግኝት ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት አቀረበ፡፡

አቶ ዳኛው ገብሩ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ በመልዕክታቸው የምንሰራው ውድ ሀብት የሆኑት ልጆቻችን ላይ ነው፤ስለዚህ ዘርፉ የሁላችንም ጉዳይ እና የሁላችንንም ትጋት የሚጠይቅ ዘርፍ ነው የትኛውም የህግ ጥሰት ሚታይበት ተቋም መቀጠል የማይችል መሆኑን በመግለፅ በጋራ በመነጋገር ውድ ሀብቶቻችንን ልጆቻችንን ብቁ እና ተወዳዳሪ በሆነ ተቋም ውስጥ ሊማሩ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

photo_2024-11-28_09-59-50 photo_2024-11-28_09-59-40

ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሃገራችን የምትፈልገውን ትውልድ ለማፍራት እና ለውጥ ለማምጣት መነጋገር፣መወያት፣መግባባት፣መናበብ እንዲሁም ህግ እና ስርዓቱን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ዜጋ ለማፍራት ወሳኝ እንደሆነ በመግለፅ ዘርፉ የትውልድ ግንባታ ስራ እንደመሆኑ በትኩረት፣ በቁርጠኝነት እና በሀላፊነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የባለስልጣኑ የእውቅና ፍቃድ እና እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ካሳ የእውቅና ፍቃድ አፈፃፀም ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በሰነዱ ላይ እንደተመላከተው በ2016 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 444 የቅድመ አንደኛ ት/ቤቶች የእውቅና ፈቃድ እድሳት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በተደረገው ምዘና፣361 ት/ቤቶች 75 እና በላይ አሟልተው የእውቅና ፈቃድ እድሳት ተደርጎላቸዋል፡፡ 5 ት/ቤቶች ከስታንዳርድ በታች በመሆናቸው የተዘጉ ሲሆን 78 ት/ቤቶች ደግሞ ስታንዳርዱን በሚጠበቀው መጠን ባያሟሉም በማስጠንቀቂያ ለአንድ ዓመት ብቻ እንዲቀጥሉ መደረጉን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

photo_2024-11-28_09-59-53 photo_2024-11-28_09-59-45

ከዚህም ሌላ በ2016 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 245 የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤቶች የእውቅና ፈቃድ እድሳት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በተደረገው ምዘና 211 ት/ቤቶች 75 እና በላይ አሟልተው የእውቅና ፈቃድ እድሳት ተደርጎላቸዋል፡፡3 ት/ቤቶች ከስታንዳርድ በታች በመሆናቸው የተዘጉ ሲሆን 31 ት/ቤቶች ደግሞ ስታንዳርዱን በሚጠበቀው መጠን ባያሟሉም በማስጠንቀቂያ ለአንድ ዓመት ብቻ እንዲቀጥሉ ተደርጓል ፡፡

ሁለተኛ ደረጃን አስመልክቶ በ2016 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 68 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የእውቅና ፈቃድ እድሳት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በተደረገው ምዘና 53 ት/ቤቶች 75 እና በላይ አሟልተው የእውቅና ፈቃድ እድሳት ተደርጎላቸዋል፡፡6 ት/ቤቶች ከስታንዳርድ በታች በመሆናቸው የተዘጉ ሲሆን 9 ት/ቤቶች ደግሞ ስታንዳርዱን በሚጠበቀው መጠን ባያሟሉም በማስጠንቀቂያ ለአንድ ዓመት ብቻ እንዲቀጥሉ መደረጉን የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡

አቶ አንዋር ሙላት የባለስልጣኑ የትምህርት ስልጠና ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የድንገተኛ ኢንስፔክሽን ግኝት ሪፖሪት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱም እንደተጠቀሰው
ኢንስፔክሽን የተቋማትን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ጠንካራ ጎኖችን በበለጠ ለማጠናከር፣ ክፍተቶችን ለማረም ወይም ለማስተካከል ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸው በዚህ መሰረት ለተቋማት የድንገተኛ ኢንስፔክሽን የተካሄደ ሲሆን ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን ለይቶ ያሳዩ ግኝቶችም ተገኝተዋል፤በተለያየ መንገድ የሚገለፁ የስርዓተ ትምህርት ጥሰቶች፣ ለመማር ማስተማሩ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶች እጥረትና ያሉትንም በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር፣ ከተሰጣቸው የእውቅና ፈቃድ ውጪ የሚያስተምሩ ት/ቤቶች መኖራቸው ዋና ዋናዎቹ የ2017 ዓ.ም ኢንስፔክሽን ግኝቶች ሲሆኑ የተጠያቂነት ሥርዓትን በማስፈን ትምህርትና ስልጠና ተቋማት እንዲስተካከሉ ማድረግ ተገቢ መሆኑን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

photo_2024-11-28_09-59-48 photo_2024-11-28_09-59-53

በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤በመርሃ-ግብሩ መጨረሻ በእውቅና ፍቃድና እድሳት የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ተቋማት እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡