ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የቴክኒክና ሙያ ብቃት ምዘና ዝግጅት አገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞች ምዘና እየተሰጠ ይገኛል የምዘና ሂደቱን አስመልክቶ የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የቴክኒክና ሙያ ብቃት ምዘና ዝግጅት አገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት የቴክኒክና ሙያ ብቃት ምዘና ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ ገነት ኃ/የሱስ የአሠልጣኞች ምዘና በተመለከተ እንደገለፁት፡-
የአሰልጣኞች ምዘና መካሄዱ ለኢንዱስትሪው ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ሠልጣኞች ብቃታቸው በተረጋገጠ አሰልጣኞች እና ግብአቱ በተሟላ ማሰልጠኛ ሠልጥነው ወደ ኢንዱስትሪው ሲገቡ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ ለመሆን እንደሚችሉ አሳውቀዋል፡፡ በሌላም በኩል የሙያ ደረጃ የስልጠና ሂደቱ ስለተቀየረ ሙያ ደረጃውን ያማከለ ስልጠና ወስደው ብቁ የሆኑ ሠልጣኞች ስልጠናው እንዲሰጡ የሚጠበቅ በመሆኑ ለአሰልጣኞች ምዘና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምዘናው ከዚህ ቀደም በተወሰኑ ሙያዎች የተሰጠ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በተለይ በሀርድ ስኪል ሙያዎች የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማሟላት እና የምዘና ጣቢያዎችን በማፍራት ወደ ምዘና የተገባበት አግባብ መኖሩን ተናግረዋል፡፡በዚህም አብዛኛው ምዘና በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እየሄደ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ በምዘና ሂደቱ ላይ ያሉ ግብአቶችን ለመቅረፍ የምዘና ጣቢያ ማፍራት፣ለምዘና ጣቢያው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን የማሳወቅ እና ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ከስራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመነጋገር ብዙ ርቀት የተሄደ ቢሆንም አሁን ላይም ያለው ነገር ሙሉ በሙሉ የተሟላ ነው ማለት ባይቻልም በሂደት ግን ችግሮቹ እየተፈቱ መሆኑን ወ/ሮ ገነት ተናግረዋል፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍ በአሰልጣኝነት ለመቀጠል አሰልጣኞች በዚህ የሙያ ብቃት ምዘና ማለፍ የግድ በመሆኑ ብቁ ያልሆኑ አሠልጣኞች ያላቸውን የክህሎት ክፍተት የሚሞላ ስልጠና በመስጠት በድጋሚ የሚመዘኑበት አግባብ መኖሩን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በተግባረ ዕድ እና በምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ አሰልጣኞችን ሲመዝኑ ያገኘናቸው መዛኞች በበኩላቸው እንደገለፁት ለአሠልጣኞች ምዘና መሰጠቱ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ጠቀሜታው የጎላ ሲሆን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያስፈልገው ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ለማብቃት የአሰልጣኞች ሙያ በየግዜው መመዘን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
እንዲሁም በምዘናው ሂደትም ብዙዎች በንድፈሃሳብ ምዘና ላይ ውጤታማ ሲሆኑ በተግባር ምዘናው ላይ ግን የክህሎት ክፍተት የሚታይበት አግባብ በመኖሩ ያላቸው ክፍተት በስልጠናዎች ሊሞሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡