ታህሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በውስጥ አቅም የተሰሩ ሁለት ጥናቶችን እና በ2016 ዓ.ም በቴ/ሙያ ኮሌጆችና ተቋማት ላይ የተሰራ የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ግኝት ለባለድርሻ አካላት አቀረበ፡፡
አቶ ዳኛው ገብሩ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ በመርሃ-ግብሩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የጥናት ውጤቶቹና የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ግኝት ይፋ መሆኑ ለተቋማችን ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም በግብአትነት ስለሚያገለግል ነው፡፡ከዚህም ሌላ በከተማችን ውስጥ ያሉ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ፖሊሲውን በአግባቡ ስለመተግበራቸው በመፈተሽ ጥራትና ተገቢነትን የምናረጋግጥበት መንገድ ነው፡፡በመሆኑም የትምህርትና ስልጠና ስራ የተናጠል ስራ ባለመሆኑ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ የባለስለጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ እንደገለጹት ብቁ ተቋም ከሌለ ብቁ ትውልድ ማፍራት አንችልም ስለዚህ ሁላችንም ይህን ጥናት እና ግኝት እንደ ግብዓት ወስደን ያሉብንን ችግሮች በማረም በአመለካከት፣ በክህሎትና በእውቀት ለሀገራችን እድገት መሰረት የሚሆን ዜጋ ማፍራት ይገባናል ብለዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ አቶ አየን ደርሰህ ባለስልጣኑ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጥ ቡድን መሪ የ2016 ዓ.ም የቴ/ሙያ ኮሌጆችና ተቋማት የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ግኝት ያቀረቡ ሲሆን በሰነዱም የ2013/14/15/16 ዓ.ም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ተቋማት የውጭ ኢንስፔክሽን ውጤት፣የኢንስፔክሽን ግኝት ንጽጽር ፣በ2016 የኢንስፔክሽን ትግበራ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች የተሰጡ መፍትሄዎች የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ባቀረቡት ሰነድ ተመላክቷል፡፡
አቶ በቃሉ ያየህ የባለስልጣኑ የትምህርት ምዘናና ምርምር ጥናት ቡድን መሪ "Factors Affecting Candidates’ Achievement on Competence Assessment In City government of Addis Ababa" በሚል ርዕስ የምርምር ግኝቶችን ያቀረቡ ሲሆን፤
አቶ አንዋር ሙላት የባለስልጣኑ ትምህርት ጥራት ማረጋገጥና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር "The status of Implementing The Standard Inspection in Technical and Vocational Institutions in Addis Ababa" በሚል ርዕስ ላይ የምርምር ግኝቶችን አቅርበዋል፡፡
በቀረቡ ሰነዶች እና የምርምር ግኝቶች ላይም ሀሳብ፣ ጥያቄ፣ አስተያየት የተነሳ ሲሆን ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል ምላሽ ለሚያስፈልጋቸውም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡በመጨረሻም በ2016 የቴ/ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ከተሰራላቸው ተቋማት መካከል የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ተቋማት የእውቅና እና ሽልማት ተካሂዷል፡፡