(ነሀሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ የ2017 መሪ እቅድ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ እቅድ የ2016 የቅንጅታዊ ትስስር ስራዎች ላይ ዛሬ በባለስልጣኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተደርጓል ፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ባለፈው በጀት ዓመት ተቋማችን ብዙ ስኬቶችን ያስመዘገበበት በተለይም ተቋማዊ ግንባታ ላይ መሠረት አድርጎ የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነበት መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በራሱ አቅም መስራት እንደሚችል እና ነገሮችን ማረም የሚችልበት መንገድ የታየበት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን, ከሁሉም በላይ በከተማ አስተዳደሩ ያሉትን ት/ቤቶች በአንድ ፖሊሲ እንዲተዳደሩ በቅድሚያ ስርዓት ማክበር እንዳለባቸው በግልፅ ውይይት የተደረገበት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ደንብና መመሪያን ባላከበሩ የትምህርት ተቋማት ላይ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ወስደን ያስተካከልንበት ለ2017 ዓ.ም የተሻለ መደላደል የተደረገበት ዓመት ነበር ያሉ ሲሆን፤ በሌላም በኩል ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ መምህራንም ብቃታቸው መረጋገጥ ስላለበት በአጠቃላይ ት/ቤት እና በቴክኒክና ሙያ የሚያሰለጥኑ አሠልጣኞችና መምህራን የተመዘኑበት ያላቸውንም አፈፃፀም የተረዱበት ዓመት እንደነበረ ተናግረዋል፡፡
አክለውም ባለስልጣኑ በሁሉም ደረጃ ስኬቶችን ያስመዘገበበት ዓመት ሲሆን ከስኬቶች ጎን ለጎን ድክመቶች በመኖራቸው እነሱን በማረም ለ2017 ዓ.ም የበለጠ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የ2016 እቅድ አፈፃፀም መሠረት አድርጎ መወያየት ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
|
በነበረው መድረክ ላይ የ2016 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የ2017 መሪ እቅድ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ እቅድ የቅንጅታዊ ትስስር ስራዎች እቅድ ሰነዶች በእቅድና በጀት ዝግጅትና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ነብዩ ዳዊት እና በለውጥና ሪፎርም ስራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ስለሺ ታደለ ቀርቧል፡፡ በቀረቡት ሰነዶች ላይ ውይይት እና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች የባለስልጣኑ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥተውበታል፡፡
በዕለቱ የቅንጅታዊ የትስስር ስራዎች ዙሪያ የትስስር የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ የተካሄደ ሲሆን በ2016 ዓ.ም በቅንጅታዊ የትስስር ስራዎች ከባስልጣኑ ጋር በጋራ ለሰሩ ባለድርሻ አካላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ በውይይቱ ላይ የማዕከልና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ስራ አስኪያጆች ዳይሬክቶሬቶች እና ቡድን መሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንደነበሩ ታውቋል፡፡